Jump to content

ሻታውኳ

ከውክፔዲያ
በ1890 ዓ.ም. ግድም ሴቶች በሻታውኳ ሙዚቃ ሲያጫውቱ

ሻታውኳአሜሪካ አገር በ1866 ዓ.ም. የተመሰረተ የትምህርት እንቅስቃሴ ነው። በተለይ የታወቀው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ሲሆን፣ አንዳንድ የሻታውኳ ተቋም እስከ ዛሬው ድረስ ስብስባ ያደርጋል። ሻታውኳ ከማስተማር በላይ ብዙ አይነት ባህላዊ መዝናናት፣ ንግግር፣ ሙዚቃ፣ ስብከት፣ ወዘተ. በማቅረቡ በተለይ ይታወቅ ነበር።

«ሻታውኳ» በየበጋው ወቅት ወራት (ጁንጁላይኦገስት) የተሰበሰበ ማኅበር ነበር። መጀመርያው ማኅበር በሻታውኳ ሐይቅኒው ዮርክ ክፍላገር ነበረ። (የሐይቁ መሃል ከጫፎቹ ይልቅ ጠባብ ስለሆነ፣ የሻታውኳ ትርጉም በኗሪዎች ቋንቋ «የታሰረ ከረጢት» ነው።) ይኸው ሻታውኳ ማኅበር «የእሁድ ትምህርት ቤት» (የክርስትና ትምህርት) አስተማሪዎች መልመጃ እንዲያገኙ የታሰበ «የክረምት ሠፈር» (ካምፕ) ነበር። መጀመርያው የሻታውኳ ተቋም የተመሠረተው በሜቶዲስት ሰባኪው ጆን ሄይል ቪንሰንት እና በንግድ ሽሪኩ ሉዊስ ሚለር ነበር። ይህም ተቋም በኒው ዮርክ እስካሁን ይገኛል።

ለቤተሠብ ሁሉ ያገለገለ የትምህርት ክረምት ሠፈር ዕጅግ የተወደደ ሀሣብ ሆኖ፣ በአስር አመታት ውስጥ የሻታውኳ ማኅበሮች በአኅጉሩ በሙሉ ቶሎ ይስፋፋ ጀመር። በአገር ቤት በባቡር በሚደርሰው ሥፍራ አጠገብ ይገኙ ነበር። በቋሚ ሥፍራዎች ከተሰበሰቡት ሻታውኳዎች በላይ፣ በየመንደሩ በድንኳኖች የሚዛወሩ ሻታውኳዎች ነበሩ። ምንም ማእከላዊ ሥልጣን አልነበራቸውም፤ ስለዚህ «ነፃ ሻታውኳዎች» ተባሉ። አብዛኞቹ ሃይማኖታዊ ወይም የክርስቲያን መርሃግብር ቢኖራቸውም፣ ሌሎች ደግሞ በተለይ አለማዊ ዕውቀትና መዝናናት ያቅርቡ ነበር።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መኪናራዲዮንፊልምቴሌቪዥንም ስለ ተፈጠሩ፤ ሕዝቡም በቀላሉ መዝናናትና ትምህርት ለማግኘት ስለ ቻሉ፣ በየጥቂቱ የዚህ አይነት መኅበር አስፈላጊነቱን ተወ። አሁን የሻታውኳ ታዋቂነት እጅግ ቀንሶ፣ ቢታወስ ለታሪካዊ ትዝታ ብቻ ይሆናል።